1 Samuel 11

ሳኦል የኢያቢስን ከተማ ታደገ

1አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ኢያቢስ ገለዓድን ከበባት፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፣ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፣ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት።

2አሞናዊው ናዖስ፣ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ።

3የኢያቢስም ሽማግሌዎች፣ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ፣ ለአንተ እንገዛለን” አሉት።

4መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5በዚህ ጊዜ፣ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከዕርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት።

6ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ እጅግ ተቈጣ። 7ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። 8ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቍጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺሕ፣ ከይሁዳም ሠላሳ ሺሕ ነበር።

9ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፣ “ለኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች፣ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለኢያቢስ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ በደስታ ፈነደቁ። 10ለአሞናውያንም፣ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው።

11በማግስቱም ሳኦል ሰራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል፣ የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳ ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ።

የሳኦል ንጉሥነት ተረጋገጠ

12ሕዝቡ ሳሙኤልን፣ “ ‘ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል!’ ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት።

13ሳኦል ግን፣ “ይህ ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን የታደገበት ቀን ስለሆነ፣ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ።

14ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፣ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውን እናጽና” አለ። 15ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በእግዚአብሔር ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት
በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል።
በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ ታላቅ በዓል አደረጉ።

Copyright information for AmhNASV